አስተምህሮት

 

የእምነት መግለጫ  

  • መግቢያ

    አዕማድ እምነቶች (አስተምህሮ)

    The Theron Life Intl Church የእምነት መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኳ የተጻፈው የመጀመሪያይቱ የሐዋርያት ቤተክርስቲያን እምነት ነው፡፡ ስለዚህ The Theron Life Intl Church ጥንታዊያኑ ታሪካዊያኑ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት ያወጧቸውን፡- የሐዋርያት፣ የኒቂያ፣ የአትናቴዎስና የኬልቄዶን የእምነት መግለጫዎች ተቀብለው በየዘመኑ የተነሱ ተሐድሶዓውያን ወደ ቀደመው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትና አስተምህሮ ለመመለስ ያደረጉትን ጥረቶች አካትተው የቆሙ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት The Theron Life Intl Church “አምስቱ ብቻዎች” በመባል የሚታወቁትን “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” “ክርስቶስ ብቻ” “በጸጋ ብቻ” “በእምነት ብቻ” እና “ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ” እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የሚጠቀሰው 'የአማኞች ሁሉ ክህነት' የተባለውን አስተምህሮ ይቀበላል፡፡

    ከዚህ በታች የተዘረዘሩት The Theron Life Intl Church ዋና ዋና የእምነት ምሶሶዎች መሠረታዊያን በመሆናቸው ወሳኞችና ዐበይት አስተምህሮ ናቸው ብለን እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    አዕማድ 1: መጽሐፍ ቅዱስ - ቃለ እግዚአብሔር

    The Theron Life Intl Church ስድሳ ስድስቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋሳዊ ቃል፤ የአማኞች የእምነታቸውና የምግባራቸው ዋና መመሪያና የመጨረሻ ባለሥልጣን እንዲሁም ማዕከል እንደሆነ ያምናል፤

    መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤የእግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡ በቅዱሳን ሰዎች አማካኝነት የተጻፈ ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና ተቆጣጣሪነት የተጻፈ ነው፡፡ ስለዚህ በውስጡ የተካተቱት እርስ በርስ የተያያዙትና የሚቀባበሉት ሁለቱም ኪዳናት የሚያስተምሩት ትምህርት ስህተት አልባና የማይሻር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የአእምሮ እውቀትና አመክንዮ ችሎታ በላይ ከግለሰቦች ገጠመኞችና ልምምዶች በላይ እንዲሁም ከቤተክርስቲያን ወግና ልምምድ በላይ የላቀ ሥልጣን ያለው፤ ሊቀነስበት ወይም ሊጨመርበት ያልተፈቀደ፤ ቤተክርስቲያንን በእውነቱ ሥልጣን የሚመራ ቃል ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የታሪክ ሂደት ልዩ ልዩ የትርጓሜ ወይም የሥነ-አፈታት መስመሮች ቢከሰቱም እውነተኛ የአተረጓጎም ሂደት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈበትን ዐውድ ያገናዘበ ከአሁኑ ዘመን ጋር ያለውን ተዛምዶ ያጤነ እና በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት የሚደገፍ መሆን እንዳለበት The Theron Life Intl Church እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    (ምሳ 30፡6፤ ሉቃ 4፡18-2፤1ጢሞ 5፡18፤ 2ጢሞ 3፡16፤ 2ጴጥ 1፡ 20-21፤ 2ጴጥ 3፡15-16፤ ዕብ1፡1-2 ዕብ 4፡12፤ ራዕ.22፡18-19፤) 2ጢሞ3፡16-17 2ጴጥ1፡20-21 2ጰጥ3፡15-16 ዩሃ17፥17

  • እግዚአብሔር አሀዱ ወሥሉስ አምላክ

    The Theron Life Intl Church በሦስት አካላት (persons) በሚኖር አንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ፤ በእግዚአብሔር ወልድ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያምናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረቱ በሆነው ርቱዕ ክርስትና የሚስጥረ ሥላሴ አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ ከዘላለም ጀምሮ፤ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ተብለው በሚጠሩ ሦስት አካላት ይኖራል፡፡ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ፍጹም አምላክ ነው፡፡

    እግዚአብሔር በሦስት አካላት ይኖራል ስንል ሦስት አማልክት ወይም መለኮቶች አሉ ማለት አይደለም፡፡ “ሦስት የሚለው ቃል ‹ስምን› ግብርን› አካልን› የሚያመለክት ሲሆን አንድ የሚለው ቃል ደግሞ ‹ባህርይን› ‹መለኮትን› እና ‹ሕልውናን› ያመለክታል፤ ስለዚህ The Theron Life Intl Church በአሀዱ ወሥሉስ አምላክ (በሥላሴ) እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    (ዘፍ 1፡26፤ ዘዳ 4፡35፤ ዘዳ.6፡4፤ 1ዜና17፡20፤ ማቴ. 3፡16፣ 28፡19፤ 1ቆሮ 8፡4-6፤ 2ቆሮ13፡14፤ 1ጢሞ 1፡12)

    እግዚአብሔር አብ

    The Theron Life Intl Church እግዚአብሔር አብ የሁሉ ፈጣሪ፣ እውቀቱና ችሎታው የማይወሰን፣ በፈቃዱ ሁሉን የሚመራ፣በሰማይና በምድር የወደደውን የሚያደርግ፤ ከልካይም ፈቃጅም የሌለው ልዑል አምላክ እንደሆነ፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን እና በፍጹም ቅድስና የሚኖር በፍቅር የተሞላ፤ ታማኝና መሃሪ አምላክ እንዲሁም ዘላለማዊ መሆኑንና ዓለምን ለማዳን አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከ አዳኝ እንደሆነ እናምናለን እናስተምራለን፡፡ (መዝ 24፡1፤ ኢሳ 45፡5-10፤ ዳን 4፡35፣ ማቴ 10፡29፤ ዮሐ 1፡18፣ 3፡16፤ ሐዋ 3፡25-26፣ 17፡26፤ 1ጢሞ 6፡15-16፤ ኤፌ 1፡1፤ 1ዮሐ 1፡18)

    እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ)

    The Theron Life Intl Church ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ አንድያ ልጅ፤ ከአብ ጋር ለዘላለም የኖረ አምላክ፤ ዓለም በእርሱ በኩል የተፈጠረ፤ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሥጋ ከድንግል ማርያም የተወለደ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ሆኖ (መለኮቱና ትስብእቱ ሳይዋዋጡና ሳይከፋፈሉ) ሁለቱን ባህርያት በአንድ አካል የያዘ፤ በምድር ላይ ያለ ኃጢአት የኖረ፤ ወንጌል እየሰበከ፤ ድውያንን እየፈወሰ፤ ሙታንን እያስነሳ፤ በጎ ሥራ እያደረገ የተመላለሰ፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ የሆነ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ የሞተ በሦስተኛው ቀን በኃይልና በክብር ከሙታን የተነሳ፤ወደ ሰማይ በክብር ያረገ፤ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ስለ እኛ የሚማልድ፤በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ በመላእክት ታጅቦ በክብርና በግርማ ወደ ምድር ተመልሶ የሚመጣ እንደሆነ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ

    The Theron Life Intl Church እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር የተካከለ አምላክ መሆኑን፤በሁሉ ቦታ የሚገኝ ፈጣሪ መሆኑን፤ አማኞችን ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ የሚያጽናና እንደ ፈቃዱም የጸጋ ስጦታዎችን ለምዕመናን የሚሰጥ፤በእነዚህ ስጦታዎቹ አማካኝነት በሁሉ ዘመን እየሠራ ቤተክርስቲያንን የሚያንጽ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክር ዓለምን ስለኃጢአት፤ ስለ ጽድቅ ስለ ፍርድ የሚወቅስ መሆኑን ያምናል፡፡ አማኞች በኃጢአት ሲመላለሱ መንፈስ ቅዱስ ማዘኑን ስለዚህ አማኞች በሕይወት ንጽሕና እንዲኖሩ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንደሚሰጣቸውና ለአገልግሎታቸውም ኃይልን እየሰጠ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ሙላት እንደሚያሳድጋቸውም እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    (ኢዮ 33፡4፤ መዝ.139፡7-10፤ ዮሐ 14፡15-16፡26፤ ዮሐ 15፡26)(ማቴ 1፡20-21፤ ሉቃ 2፡5-7፣ 3፡16፤ ዮሐ1፡14-18፣ 6፡68-69፣ 8፡58፤ 1ቆሮ 1፡30፤ ቆላ 1፡1-4፣ 3፡1፤1ጢሞ 2፡5፤3፡16፤ 1ዮሐ 1፡1-3፤ዕብ 13፡ 8) ዘዳ6÷4 ኢሳ44÷6-8 ዮሐ5÷44 ሮሜ3፥30 1ቆሮ8፥4-7  ገላ3፥20  ኤፌ4፥5-6  1ጢሞ1፥17 1ጢሞ2፥5 ይሁ1:25  ኢሳ48:16-17 ማቴ28:19-20 ሐዋ5÷3-4 ኢሳ9÷6 ዮሐ1÷1 ሮሜ9÷5 (መዝ 24፡1፤ ኢሳ 45፡5-10፤ ዳን 4፡35፣ ማቴ 10፡29፤ ዮሐ 1፡18፣ 3፡16፤ ሐዋ 3፡25-26፣ 17፡26፤ 1ጢሞ 6፡15-16፤ ኤፌ 1፡1፤ 1ዮሐ 1፡18)

  • የሰው ማንነት ሁኔታ

    The Theron Life Intl Church ሰው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን፤ በኃጢአት መውደቁንና በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ያለበት በደለኛ መሆኑን ያምናል፡፡

    The Theron Life Intl Church ሰው በእግዚአብሔር አምሳል በመፈጠሩ አምላክ በሉዓላዊነቱ በሚያስተዳድረው ፍጥረት ውስጥ ምድርን የመጠበቅና የማልማት አደራና ኃላፊነት የተቀበለ ክቡር ፍጡር እንደሆነ፤ ሰው በፍጥረቱ በዕውቀቱና በችሎታው ውስን የሆነ፤ መለኮትነት የሌለው፤መጽሐፍም እንደሚል “ከእግዚአብሔር ሕይወትና እስትንፋስ እየተቀበለ የሚኖር በእግዚአብሔር ላይ ተደጋፊ ፍጡር እንደሆነ፤ ሰው ከምድር አፈር በመበጀቱና የእግዚአብሔር እስትንፋስ በውስጡ በመኖሩ ቁሳዊም፣ መንፈሳዊም ማንነት ያለው ፍጡር መሆኑን፤ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ወይም ትዕዛዝ ችላ በማለት የራሱን ፈቃድ በተከተለ ጊዜ በኃጢአት መውደቁና ኃጢአትም ወደ ምድር መግባቱን፤ ከዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ቀውስ ጠብና መለያየት፤ በሽታና ስቃይ ጭንቀትና መከራ ሞትም መከሰቱን፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ በኃጢአት ምክንያት በሰው ልጅ ላይ እንደደረሰ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    (ዘፍ 1፡26-27፤ ዘፍ 2፡7፤ ዘፍ 2፡21-22፤ ዘፍ 3፡16-19፤ ኢዮብ 10፡8፤ ኢዮብ 33፡4፤ መዝ 100፡3፤ ኢሳ 42፡5፣ 45፡12፤ ኤር 27፡5፤ ሐዋ.17፡ 24-27፤ ራዕይ 4፡11) ዘፍ 1፡26-27 ዘፍ 2፡7  1ተሰ5፥23 ዘካ12፡1 ኢሳ57፡15-16 ዕብ4:11-12

  • የሰው ልጆች ድነት (መስቀለ ክርስቶስ - የድነት ጎዳና)

    The Theron Life Intl Church ሰው ከኃጢአት ዕዳ ኃይልና ቅጣት ሊድን የሚችለው ኃጢአት የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ምትክ ሆኖ በመስቀል ላይ በፈጸመው የቤዛነት ሥራ ብቻ በመሆኑ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሚጸድቅ ያምናል፡፡

    The Theron Life Intl Church የሰው ልጅ በራሱ ሥራም ይሁን በሌሎች ፍጥረታት እርዳታ በኃጢአት ምክንያት ከመጣበት የእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን ስለማይችል ድነት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት መሆኑን፤የክርስቶስ መስቀል የሰው ልጅ ድነት ሙሉ ለሙሉ የተከናወነበት ቦታ እንደሆነ፤ ክርስቶስ በመሞቱና በመነሳቱ የዘላለም ሕይወት ዋስትና መገኘቱን ያምናል፡፡

    The Theron Life Intl Church መስቀሉ የወንጌል ማዕከል መሆኑን የመስቀሉም መንገድ የኑሮአችን መርሕና ዘይቤ እንደሆነ ማለትም በመስጠት ማግኘት የሚስተናገድበት ከሁሉ ኋላ በመሆን ፊተኛ የሚኮንበት፤በድካም ብርታት የሚገለጽበት፤ ስለዚህም በውርደት ክብር የሚለበስበት የሕይወት ቅኝት መሆኑን ያምናል፡፡

    The Theron Life Intl Church ሰው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን በመንፈስ ዳግም በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን፤ አዲስ ፍጥረትም እንደሚሆን፤ ከእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ድኖ የክርስቶስን ጽድቅ እንደሚጎናጸፍ ያምናል፡፡ ይህም አዲስ ፍጥረት በጽድቅና በቅድስና የተቃኘ አዲስ የሕይወት ዘይቤ ይከተላል፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሓፍ እንደሚያስተምረው “መንፈሱም፣ ነፍሱም፤ ሥጋውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለነቀፋ ፈጽሞ እንዲጠበቅ” በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሁለንተናው በቅዱስ ኑሮ የተመራ ሰው እንደሚሆን ያምናል፡፡

    The Theron Life Intl Church እንደሚያምነው ኃጢአት አመጽ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያለመታዘዝና ሕግን የመተላለፍ ተግባርም ነው፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ ውጭ የመሆን ኑሮ ነው፡፡ የኃጢአትም ደመወዝ ሞት ነው፡ ፡ Apostle Born Ministries በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው ኃጢአት ሊያደርግና በኃጢአት ሊኖር እንደማይገባው ያምናል፡፡ ነገር ግን አማኝ ኃጢአት ቢያደርግ በእውነተኛ ኑዛዜና ንስሐ ወደ ጌታ ቢመለስ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነጻው እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    (ኢሳ 53፡1-12፤ ዮሐ 3፡16፤ ሮሜ 3፡25፣ 8፡3-4፤ ኤፌ 2፡5-6፤ 1ተሰ 4፡2፤ ቲቶ 2፡11-15፤ 1ዮሐ 1፡7-10፣ 4፡10፣ 5፡23) ኢሳ53 ፡1-12  ኤፌ2፡5-9 ዮሐ3፡16-17 ሮሜ3፡25 ቲቶ2፡11 ሮሜ8፡3-4

  • ቤተ ክርስቲያን

    The Theron Life Intl Church ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም የተወለዱ አማኞች ሁሉ በሚገኙባትና የኢየሱስ ክርስቶስ አካል በሆነች በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ያምናል፡፡ 'ቤተ ክርስቲያን' የሚለው ቃል ትርጉም የክርስቲያን ወገን ወይም የክርስቲያን ማኅበረሰብ ማለት ሲሆን ቃሉ በቁሙ ሲወሰድ ሕንጻን የሚያመለክት ቢመስልም በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ግን ቤተ ክርስቲያን ማለት ማህኅበረ ክርስቶስ እንደሆነ ያምናል፡፡

    የቤተ ክርስቲያን መሥራች እና ጀማሪዋ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ፤ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጀች በመንፈስ ቅዱስ ለቤዛ ቀን የታተመች ፤ በቃሉና በመንፈሱ እየነጻችና እየታነጸች የምትገሰግስ ሠራዊት መሆኗን ያምናል፡፡

    The Theron Life Intl Church ቤተክርስቲያን በክርስቶስ በተገለጠው የወንጌል እውነት ላይ የቆመች ይህንኑ የመዳን ወንጌል ለዓለም ሁሉ ልታውጅ በሕይወቷም ልትገልጸው የተጠራች ባለ ተልእኮ ማኅበረሰብ እንደሆነችና አገልግሎቷን በትህትናና በቅንነት እንዲሁም በተገቢው ሥርዓት ማከናወን እንዳለባት ያምናል፡፡

    ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ አንድነት የምትመላለስ የጌታ እራትና ቅዱስ (የውኃ) ጥምቀት በሚባሉ ቅዱስ ሥርዓቶች አንድነቷን እየገለጸች፤ የቤተ ክርስቲያን ራስ ከሆነው ከክርስቶስ በተቀበለችው ሥልጣን ምዕመኗንን እያስተዳደረችና እየመራች በዓለም ከሚገኝ ዕድፍ ራሷን እየጠበቀችና በጎ ምግባርን እያበረታታች እስከ ጌታ ምጽአት ቀን ድረስ በዚህ ምድር የምትቆይ የክርስቶስ አካል እንደሆነችም ያምናል፡፡

    እንዲሁም አማኞች የአምላካቸውንና የጌታቸውን የቸርነትና የበጎ ምግባር አርአያነት ተከትለው በምድር ተንሠራፍቶ ያለውን የሰውን ልጅ መንፈሳዊ ሥነ-ልቦናዊ ቁሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ ሥቃይ የሚካፈሉ ችግሩን ለማቅለልም በቅን ልቡና የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ በቅዱስ ቃሉም ስለ ሥራ ትጋት የተሰጠውን መመሪያ ተቀብለው፤ በግልም ሆነ በኅብረት ለሥራ የተነቃቁ፤በታማኝነት እና በትጋት የሚያገለግሉ ሊሆኑ እንደሚገባ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    (ማቴ 16፡18፣ 25፡34-40፤ ሐዋ 20፡28፤ ሮሜ 12፡5፣ 1ቆሮ 3፡11፣ 10፡ 16-17፤ 2ቆሮ 1፡22፤ ገላ 1፡8፣ 3፡28፤ እና 12፤ ኤፌ 4፡13፤ ያዕ.2፡14-17፤ ራዕ 1፡5፣) ሐዋ11:26 1ቆሮ3:16-17 ሐዋ4፥32-35 ፊል1፥27-28 ሐዋ12፥1-12

  • የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአትና የዓለም መጨረሻ

    The Throne Life intl Church በዝግጅት፣ በንጥቀት፣በመከራው ዘመን፣ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት፣ በሺህ አመት መንግሥትና በዘላለም ፍርድ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እወስዳችኃለሁ ብሎ ተስፋ እንደሰጠን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ ሄደ እንደዚሁ በአካል ተመልሶ ወደ ምድር እንደሚመጣ፤ የሙታንም ትንሣኤ እንደሚሆን እናምናለን። በመጨረሻም ፍርድ ኃጥአን ወደ ዘላለም ቅጣት ሲሄዱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የሞቱና በመምጣቱም ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ አማኞች ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚሄዱ ይህም ለአማኞች የተባረከና በንቃት ሊጠብቁት የተገባ ተስፋቸው እንደሆነ እናምናለን እናስተምራለን።

    (ማቴ.24፡36-42፤ ዮሐ.14፡1-3፤ ሐዋ.1፡11፤ 1ተሰ.5፡2፤ ራዕ.19፡11-16፤ 20:11-15 22:12-15) ዩሃ14፥1-3 1ተሰ4፥13-18 1ተኛ3፡12-13 ራዕ20:4 ማቴ25፡40-42 

  • ቅዱሳን ኪሩቤሎችና የወደቀው ኪሩቤል ያሁኑሰይጣን እንዲሁም ቅዱሳን መላእክትና የወደቁ መላእክት

    The Throne Life Intl Church እንደሚያምነው ቅዱሳን ኪሩቤሎችና ቅዱሳን መላእክት መንፈሳውያን ፍጥረት ሲሆኑ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ በሰማይና በምድር ላይ የእርሱን ዓላማ የሚያስፈጽሙ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ኪሩቤሎቹ በዙፋኑ ዙሪያ ያሉና የሚጋርዱ፣ የሚያመልኩ በፍርድ ጊዜም የሚገለጡ፣ እንደሆኑና በአፈጣጠራቸውም ከመላእክት የተለዩ መሆናቸውን፤ መላእክቱ ደግሞ የሚያምኑትን ቅዱሳን ሰዎች ለመርዳት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላኩ ከሰው ልጆች ዕውቀትና ችሎታ በላይ ኃይል የተሰጣቸው በአምላክ ፊት መልዕክት ለመቀበል የሚቆሙ ፍጥረት መሆናቸውን፡፡

    የወደቁ መላእክት የተባሉት የጨለማው ዓለም ገዢ በተባለው በመሪያቸው በዲያቢሎስ ወይም ሰይጣን አለቅነት የሚንቀሳቀሱ የክፋት መንፈሳዊያን ሠራዊት መሆናቸውን፤ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ከዚህ የጨለማ ሠራዊት ጋር በብርቱ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሲሆን “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብርታት ድል በመንሳቱ እንደምንዞርና እንደምንቀጠቅጥ እናምናለን እናስተምራለን።

    (ማቴ. 28፡2-7፣ 18 ፤ ሉቃ.9፡1፣ 10፡17-20፤ ኤፌ.6፡10-18፤ ቆላ.1፡16፤ 1ጢሞ.3፡16፤ ዕብ.1፡14፤ 1ጴጥ.5፡8-9፣ 2ጴጥ.2፡4፣ 11፤ ይሁዳ 6 ያዕ.4፡7)መዝ104:1-4 ሕዝ28፡13-15 ራዕ5:11 ሉቃ10:18-20

  • The Theron Life Intl Church በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚደረግ እግዚአብሔር የቀደሰው መሆኑን እና የአንድ ሥጋ ኪዳን እና የማይፈርስ ጥምረት ሆኖ በእግዚአብሔር እንደተጀመረ እናምናለ። 

    ጋብቻ በተቃራኒ ጾታዎች ብቻ ማለትም በአንድ ወንድና ሴት መካከል ብቻ የሚፈጸም ክቡር የአንድነት ኪዳን መሆኑን፤ ተጋቢዎችም በፍቅርና በታማኝነት ለእግዚአብሔር ክብር መኖር እንደሚገባቸው እናምናለን እናስተምራለን፡፡

    ዘፍ2:20-25 ማቴ19፥3-9